[Amharic Version] UNAIDS Orthodox Clergy Pocket Book

60
ፍቅረ-ቢጽ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት የተዘጋጀ ማስታወሻ

Transcript of [Amharic Version] UNAIDS Orthodox Clergy Pocket Book

ፍቅረ-ቢጽ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት የተዘጋጀ ማስታወሻ

2

የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን መልእክት በሃይማኖት መሪዎች እና ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ሰዎች መካከል የሚደረግ ውይይት የኤችአይቪን ሥርጭት በመግታት ላይ እና እስከ አሁንም የተጋረጡትን መሰናክሎች ለማስወገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ ስለዚህ ኢኩሜኒካል አድቮኬሲ አሊያንስ (EAA)፣ ዘ ግሎባል ኔትወርክ ኦፍ ፒፕል ሊቪንግ ዊዝ ኤችአይቪ (GNP+)፣ ዘ ኢንተርናሽናል ኔትወርክ ኦፍ ሪሊጂየስ ሊደርስ ሊቪንግ ዊዝ ኤንድ አፌክትድ ባይ ኤችአይቪ (INERELA+) እና ዩ.ኤን.ኤይድስ (UNAIDS) በመተባበር ይህንን በሃይማኖት መሪዎች እና ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝባቸው ሰዎች መካከል የሚደረገውን ውይይት ለመደገፍ ማኅበራዊ ማዕቀፍ ለውይይት የተሰኘውን መመሪያ አዘጋጅተዋል፡፡

2

3

ይህ የተውጣጣ መረጃ እንዲዘጋጅ መንገድ የከፈተው ይኸው ማኅበራዊ ማዕቀፍ ውይይት የተጀመረው በኢትዮጵያ በ2005 ዓ.ም. አጋማሽ ሲሆን ከኢኩሜኒካል አድቮኬሲ አሊያንስ እና ዩ.ኤን.ኤይድስ የገንዘብ እና የሙያ እገዛ ተደርጎለታል፡፡

ይህ የዐውዳዊ ስብከት መመሪያ ፍቅረ - ቢጽ በሚያዝያ ወር 2005 በኢትዮጵያ የተደረገው የማኅበራዊ ማዕቀፍ ለውይይት አካል የሆነው የመጀመሪያው የገጽ ለገጽ ውይይት ውጤት ነው።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን (EOTC-DICAC) ይህ ፕሮጀክት ይሳካ ዘንድ የገንዘብ እና የሙያ ድጋፋቸውን ላደረጉ አጋሮች ሁሉ ምስጋና ለማቅረብ ይወዳል፡፡

4

የቅዱስ ፓትርያርኩ መልእክት

“ወዘሰ ያፈቅር ቢጾ ውስተ ብርሃን ይነብር፤ ወአልቦ ዕቅፍት በኀቤሁ፤ ወንድሙን የሚወድ ግን በብርሃን ይኖራል በእርሱ ዘንድ መሰናክል የለም’’ 1ዮሐ. 2፥10

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በጕልኅ እንደሚያስገነዝበው አምጻኤ ዓለማት እግዚአብሔር የሰው ልጆች በሕግ እና በሥርዓት እንድንተዳደር ዐሠርቱ ትእዛዛትን ሰጥቶናል፡፡ ሕጉም ፍቅረ እግዚአብሔር እና ፍቅረ-ቢጽ ተብሎ በሁለት ይከፈላል ማቴ. 22፥37-40፡፡ ይህ ሕገ እግዚአብሔር

5

ለፈጣሪያችን በመገዛት እና ባልንጀሮቻችንን ሳናሳዝን ይልቁንም ለእነርሱ መልካም ተግባራትን እያደረግን የአምላካችንን ትእዛዝ በፍቅር የምንፈጽምበት ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ማንም ሰው ላይ በምንም ምክንያት አድልዎ እና መገለል እንዳይደርስበት ስታስተምር ኖራለች፡፡ በተለይም የኤድስ ቫይረስ በደማቸው የሚገኝ እና በበሽታው ምክንያት የታመሙ ወገኖች አድልዎም ሆነ መገለል እንዳይደርስባቸው ከማስተማር ባሻገር በምትሰጠው አገልግሎት ሁሉ አትለይም፡፡በበሽታው ምክንያት ለተጎዱ ሕሙማን እና ወላጆቻቸውን በሞት ላጡ ሕጻናት ተገቢውን ድጋፍ እና እንክብካቤ በማድረግ ላይ ስትሆን በሌሎች አካላትም እንዲደረግላቸው ዘወትር ታሳስባለች፡፡

ስለ እግዚአብሔር ያለንን ፍቅር መግለጽ የምንችለው በተግባር ስለሆነ እሱን አብነት አድርገን ሰውን በሰውነቱ በመውደድ ለሁሉም ሰው የፍቅርን ምሥጢር በተግባር መግለጽ እንደሚኖርብን፥ ራሳችንን በራሳችን ለመጠየቅ ነው። ኀጢአት ለሰው ልጅ ጐጂ በሽታ ነው። ይህ ሲሆን የእግዚአብሔር ልጅ ወደዚህ ዓለም የመጣው ለበሽተኞች እንጂ ለጤነኞች አይደለም፥ (ማቴ. 9፥12)። ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ በእርግጥ ፍቅረ እግዚአብሔርና ፍቅረ ቢጽ ያለን መሆኑን ማረጋገጥ የሚገባን ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ለሚገኝባቸው ወገኖቻችን በምናደርገው እንክብካቤና በምናሳየው ርኅራኄ መሆን ይኖርበታል። በሽታው በምንም ዓይነት መንገድ

6

ይምጣ እነሱን ከማኅበራዊ ኑሮ ግንኙነት ማግለል የክርስቲያን ሥራ አይሆንም። በሽታውን አክብዶ በመናገር ሕሙማኑን ተስፋ ማስቆረጥም ራሱ ኀጢአት ነው፤ በደልም ነው፤ የጠላትነት እንጂ የፍቅር ተግባር አይደለም። ይልቁንም የተሰበረ ሕሊናቸውን በሚያጽናናና በሚያበረታታ ቃል መጠገን ግዴታ ይሆናል። ፍቅርን በተግባር መግለጽ የሚቻለውም ይህ ሲሆን ነው። በሌላ በኩል ሕጻናት ከቫይረሱ ጋር እንዳይወለዱ ለእናቶች ተገቢው እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ነፍሰ ጡር እናቶች ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ተገቢውን ክትትል ሊያደርጉ፣ በጤና ተቋማትም በባለሙያዎች እገዛ መውለድ፣ ድኅረ ወሊድ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ካህናት ምክር መለገስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ በቤተ ክርስቲያን ልደት ላይ ከነበሩ አንድ መቶ ሃያ ቤተሰቦች መካከል በድንቅ አጠራሩ የጠራቸው ፤ በክብር የጎበኛቸው ሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት በአባልነት ነበሩ፡፡ ይህ የሚያሣየን በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሴቶች እኩልነት ፣ ሚና ወይም አስፈላጊነት ጕልኅ መሆኑን ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ውስጥ እንዲህ ዓይነት ቦታ ያላቸው እናቶችና እህቶችን እና ሴት ልጆችን ጾታዊ ጥቃት ሲደርስባቸው ዝም ብሎ ማየት ለእግዚአብሔር ቃል አለመታዘዝ እንደሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡

በአጠቃላይ መጽሐፍ “እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤’ ማቴ. 7፥12 እንዲል የቤተ ክርስቲያናችን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ከዩ.ኤን.ኤድስ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ያዘጋጀው

7

ይኽንን መጽሐፍ በመጠቀም ካህናት የንስሓ ልጆቻችሁን እና ሌሎች ምእመናንን እንድታስተምሩ በልዑል እግዚአብሔር ስም አሳስባለሁ፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ! አባ ማትያስ፤

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፤ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵሱም፤ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤

8

የልማት ኮሚሽኑ ሊቀ ጳጳስ መልእክት

“ወአንትሙሰ ከመ አግብርተ እግዚአብሔር ኵሎ አክብሩ፤ ወቢጽክሙኒ አፍቅሩ፤ ወለ እግዚአብሔርኒ ፍርህዎ፤ እናንተስ የእግዚአብሔር አገልጋዮች እንደመሆናችሁ ሁሉን አክብሩ፥ ወንድሞችን ውደዱ፥ እግዚአብሔርን ፍሩ፥’ (1 ጴጥ. 2፥17) ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ይኽንን ቃል የተናገረበት መሠረታዊ ምክንያት ለወንድሞቻችን ቢርባቸው

እንድናበላቸው፣ ቢጠማቸው እንድናጠጣቸው፣ ከልብስ ቢራቆቱ እንድናለብሳቸው በአጠቃላይ በጎ ነገር እንድናደርግላቸው ለማሳሰብ ነው፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በልማት ኮሚሽኑ በኩል ሁሉም ሰዎች ያለ አድልዎ የሚያስፈልጋቸው መሠረታዊ ነገሮች እንዲሟላላቸው ከአጋሮች ጋር በመተባበር

9

በሁለገብ ልማት ላይ ስትሳተፍ ከ40 ዓመታት በላይ ሆኗታል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ለሰው ልጆች ፈታኝ ከሆኑት በሽታዎች መካከል ዋነኛው ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ሲሆን፤ በሽታው መከሰቱ በይፋ ከታወቀ ጀምሮ አስከፊነቱን በመከላከል፣ ለሕሙማን እንዲሁም ለወላጅ አጥ ሕጻናት እና ቤተሰቦቻቸው ድጋፍ እና እንክብካቤ በመስጠት የበኩሏን አስተዋጽኦ አበርክታለች፡፡

አሁን ባለንበት ወቅት የበሽታው ስርጭት የቀነሰ ቢሆንም ከምድረ-ኢትዮጵያ ባለመጥፋቱ፣ ፀረ-ኤች.አይ.ቪ መድኃኒቱን የሚወስዱ ሕሙማን በመኖራቸው፣ ከቫይረሱ ጋር የሚወለዱ ሕጻናት ቁጥር በሚፈለገው ሁኔታ ባለመቀነሱ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ጾታዊ ጥቃት የሚደርስባቸው ወገኖቻችንም ስላሉ “ፍቅረ ቢጽ’ የተባለውን አነስተኛ መመሪያ በማዘጋጀት ትምህርቱ በሠፊው እንዲዳረስ ጥረት በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡

እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት ፍቅር ማለት የተቸገሩትን መርዳት ነው፣ ለተራቡ ማጉረስ ፣ለተራቆቱት ማልበስ፣ ጠላትን መውደድ፣ የታመሙትን መጎብኘት፣ የደከሙትን መርዳት፣ ያዘኑትን ማጽናናት፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ የመረዳዳት እና የመተሳሰብ ባሕል አንዲዳብር ጠቃሚ ያልሆነዉ ጎጂ ልማድ አንዲወገድ ማድረግ ከፍቅርም በላይ ፍቅር ነው ከአገልግሎት በላይ ክቡር አገልግሎት ነው “እውነት እላችኋለሁ ከእነዚህ ከወንድሞቼ አነስተኛ ለሆነው ለአንዱ እንኳ ያደረጋችሁት ሁሉ ለአኔ እንዳደረጋችሁ ነው” ተብሏልና

10

(ማቴ 25፥40) በአሁኑ ጊዜ የኅብረተሰቡን እርዳታ ከሚፈልጉት ወገኖች መካከል የኤድስ ሕሙማን ስለሆኑ እነርሱን መርዳት፣ መንከባከብና ለእነርሱ የቸርነት ሥራ መሥራት «ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ» የሚለውን ሕግ መፈጸም ነው። በመሆኑም መጽሐፏን ካህናት እንደመመሪያ በመጠቀም የንስሓ ልጆቻቸውን እንዲያወያዩበት፣ እንዲያስተምሩበት እና እንዲመክሩበት በቤተክርስቲያናችን ስም አሳስባለሁ፡፡

ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን!

አባ ሳሙኤል፤

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል

11

ሀ. ዐውድ፦ ሁኔታዎችን ማጥናት

በታሪክ ውስጥ ሕመም ሁልጊዜም ከአሉታዊ አስተሳሰብ እና ከማግለል ጋር ይያያዛል። ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በምድር ላይ በነበረበት ዘመን ይህንን አስተሳሰብ እና ድርጊት የተቃወመ ሲሆን እኛም ይህንኑ ልናደርግ በጠራበት ፍቅር እንዲኖሩ በማሳሰብ ይህንን ሁኔታ መታገል ይገባናል።

አሁን ያለንበት ዘመን ሁኔታዎች ፈፅመው ተለዋውጠዋል፣ በእኛ ዘመን ልጆች ከኤች.አይ.ቪ ጋር ይወለዳሉ፤ ነገር ግን ይህንን መከላከል እንችላለን። በመሆኑም ልጆቻችን ጤናማ ይሆኑ ዘንድ የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤ ለመስጠት ተገቢውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅብናል።

ዛሬ ወላጆች አዲስ የሚወልዷቸው ልጆች ከኤች.አይ.ቪ ጋር እንዳይወለዱ ተገቢውን የህክምና ክትትል ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

፩ የጥናት ዳራ

12

13

ትዳር ክቡር እና መኝታውም የተቀደሰ ነው፣ ይህ የትዳር ግንኙነት በፍቅር እና በርህራሄ ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበት አምላካችን እግዚአብሔር መመሪያ ሰጥቶናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሁሉም ፍቅርን ያሳየበት መንገድ ለሰው ዘር ሁሉ አርአያ ይሆናል። በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት ተቀባይነት የሚሰጠው የግንኙነት ገጽታ ካለመሆኑም ባሻገር የሴቶችን አካል፣ ስሜት እና ሥነ- ልቡና ይጎዳል። ትዳራችን በእግዚአብሔር ቃል እንደተመሠረተ ስንረዳውና የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥሪ መሆኑን ስንረዳ እና ስናውቅ ግንኙነቶቻችን ሁሉ በፍቅር እና በርህራሄ ላይ እንደ ተመሠረቱ እናረጋግጣለን።

ፍቅር እና እንክብካቤ ለሁሉም ሰው የሚያስፈልግ ቢሆንም በይበልጥ መገለል ለደረሰባቸው እና ፈተና ለገጠማቸው ሰዎች እንክብካቤና ድጋፍ ማድረግን ጨምሮ ፍቅር እና ርህራሄ በአግባቡ ማድረግ ያስፈልጋል። ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ላዘኑ መጽናናትን፣ ለታመሙ ፈውስን፣ ለተራቡ ምግብን፣ ለተጨነቁ ሰላምን በመስጠት ያረጋጋቸው ነበር፡፡ በኋላም ሐዋርያትን ሸክማቸው የከበደባቸውን ሰዎች ሸክማቸውን አቅሉላቸው፣ የታመሙትን ፈውሱ፣ የተጨነቁትን አረጋጉ በማለት ስልጣን ሰጥቷቸዋል፡፡ ክርስቶስ ሳያደርግ አድርጉ ያለን አንዳችም ነገር የለም ይልቁንም እርሱ በማድረግ እንድናደርገው አሳየን፡፡

ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ እና እንክብካቤ መስጠት አካላዊ ድጋፍ ከማድረግ አልፎ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያስከትሉ አስተሳሰቦችን ከማኀበረሰቡ መካከል ማስወገድ እና ማኅበራዊና ስነ-ልቦናዊ ድጋፍ ማድረግን ያካትታል::

14

15

ለ. ይህንን በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ታማሚዎች ተቀባይነት ማጣት፣ መድልዎና መገለል ላይ ያተኮረ የመመሪያ መጽሐፍ ማዘጋጀት ያስፈለገበት ምክንያት

የሃይማኖት መሪዎች ጉዳዩን በሚገባ ተረድተው ተሳታፊ መሆናቸው ለኤች.አይ.ቪ የሚሰጠውን ምላሽ ውጤታማ የማድረጉ ሂደት ወሳኝ አካል ነው፡፡ በተመሳሳይም፣ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝባቸው ሰዎች ንቁና ትርጉም ያለው ተሳትፎ ማድረጋቸው ለኤች.አይ.ቪ በሀገር፣ በክልል እና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለሚሰጠው ምላሽ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አለው፡፡ ነገር ግን፣ በእነዚህ ሁለት ባለ ድርሻ አካላት መካከል ከሚደረገው ውይይት እና መተባበር መካከል ፈታኝ ሁኔታዎችን ለማስወገድ፣ ከስኬታችን ለመማርም ሆነ የተማርናቸውን ትምህርቶች ለሌሎች ለማስተላለፍ ድጋፍ እና ምሪት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም የተነሳ፣ ኢኩሜኒካል አድቮኬሲ አሊያንስ (EAA)፣ ዘ ግሎባል ኔትወርክ ኦቭ ፒፕል ሊቪንግ ዊዝ ኤች.አይ.ቪ (GNP+)፣ ዘ ኢንተርናሽናል ኔትወርክ ኦቭ ሪሊጂየስ ሊደርስ ሊቪንግ ዊዝ ኤንድ አፌክትድ ባይ ኤች.አይ.ቪ (INERELA+) እና ዩ.ኤን.ኤይድስ (UNAIDS ) በቅርቡ ይህንን በሃይማኖት መሪዎች እና ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ በሚገኝባቸው ሰዎች መካከል የሚደረግ ውይይት እና የጥምረት እንቅስቃሴ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመደገፍ የሚያስችል መመሪያ አስተዋውቀዋል፡፡ ማኅበራዊ ማዕቀፍ ለውይይት የተሰኘው ይህ መመሪያ በእያንዳንዱ ሀገር ከኤች.አይ.ቪ ጋር የሚኖሩ ሰዎችን በቁጥር የያዘና የአኗኗር ሁኔታቸውን የሚያብራራ ሲሆን፣ ሁለቱንም የሃይማኖት መሪዎችንም ሆነ ከኤች. አይ.ቪ ጋር የሚኖሩ ሰዎችን ያለውን ማስረጃ በመተንተን የጥምረት እንቅስቃሴ የሚስፈልግባቸውን አቅጣጫዎች ለይተው እንዲያውቁ እና ለቀጣይ ውይይት የሚጠቅሙ ቁልፍ አጀንዳዎችን እንዲለዩ ያግዛል፡፡

16

ይህ ማኅበራዊ ማዕቀፍ ለውይይት በኢትዮጵያ የተጀመረው በ2005 ዓ.ም አጋማሽ ሲሆን የመጀመሪያው የገጽ-ለገጽ ውይይት የተደረገው በሚያዝያ ወር ነበር፡፡ ስብሰባውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክን ጨምሮ 50 ሰዎች ተካፍለውታል፡፡ በስብሰባው ጊዜም 11 ክትትል የሚያስፈልጋቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች እንዲሁም ተጨማሪ ውይይት የሚጠይቁ 3 አቅጣጫዎች (ሥነ-ጾታ፣ ወጣቶች እና ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች) ተለይተው ታውቀዋል፡፡

ማኅበራዊ ማዕቀፍ ለውይይት በኢትዮጵያ ውስጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአነስተኛ የሥራ ጥምረት ቡድን አጋዥነት የሚደረግ ሲሆን ተገቢውን የዕቅድ፣ የክትትል እና ሚዛናዊ ቀጣይ ውይይት ለማካሄድ የሚያስችሉ ስድስት ቁልፍ አካሄዶችን ተግባራዊ የሚያደርግ ነው፡፡ ስለዚህ፣ የቴክኒክ ድጋፍ የሚያደርግላቸው የሥራ ጥምረት መገለልን የሚገታ ፣ ጾታዊ እኩልነትን የሚያረጋግጥ እንዲሁም ኤች.አይ.ቪ ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፍበትን መንገድ የሚያስቀር ትምህርት ለሃይማኖታዊ ተቋማት እንዲዘጋጅ ወስኗል፡፡

17

18

19

ሐ. ኤች.አይ.ቪን ለመከላከል የካህናት ሚና

ካህናት አባቶች አቅጣጫን የሚያመላክቱ ናቸው። ካህናት ለማኅበረሰቡ የሚጎዳ እና የማይጎዳውን ልማድ እየለዩ በመንገር እና በየትኛው አቅጣጫ መጓዝ እንዳለበት አቅጣጫ ጠቋሚ በመሆን ሰዎች በየትኛው መንገድ ሊጓዙ እንደሚገባ የሚያሳዩ መልእክተኞች ናቸው። ከዚህም ባሻገር ካህናት በማኅበረሰቡ መካከል የሚገኙ ፈታኝ ሁኔታዎችን ነቅሶ በማውጣት እና ችግሮችን በመፍታት በድርጊታቸው እና በእሳቤያቸው የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር ይገልጣሉ። ይህ መመሪያ የሃይማኖት መሪዎች ከፍተኛውን የመሪነት ሚና በመጫወት ማኅበረሰባቸውን ሊደግፉ የሚችሉባቸውን እንደ አድልዎና መገለል፣ የኤች. አይ.ቪን ከእናት ወደ ልጅ መተላለፍ በመግታት ከቫይረሱ ነጻ የሆኑ ልጆች እንዲወለዱ በማድረግ፣ የሴቶች ጥቃት እንዲሁም ለሕሙማን ስለሚሰጡ ድጋፍ እና እንክብካቤ ያሉ ጉዳዮችን ይዘረዝራል።

20

፪. በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ምክንያት የሚደርሱ አድልዎ፣ መገለል እና አለመቀበል ላይ የሚደርስ

ሀ) ዐውድ

በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ከሠላሳ ሚሊየን የሚበልጡ ሰዎች ከኤች.አይ.ቪ ጋር ይኖራሉ። ኤች.አይ.ቪ. ኤድስ እስከ አሁን ድረስ በዐሥር ሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን፣ ይህም ወደ ሃያ ሚሊየን የሚገመቱ ህጻናትን ያለ ወላጅ አስቀርቷል። በዐሥር ሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎችም የእነዚሁ ሰዎች ወዳጆች፣ ወላጆች፣ ልጆች እንዲሁም ጎረቤቶች ከመሆናቸው የተነሳ የጉዳቱ ተጠቂ ናቸው።

በዓለማችን ላይ ከፍተኛው ቁጥር ያላቸው በኤች.አይ.ቪ የተጠቁ ሰዎች ከሚኖሩባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት። ይህንን ልንረዳ የሚገባን ግን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ነው። በኢትዮጵያ ከሰማንያ ሚሊየን የሚበልጡ ሕዝቦች አሉ ስለዚህ፣ ሁለት በመቶ የሚያህለው ዜጋ እንኳ ተጠቂ ቢሆን ቁጥሩ እጅግ የበዛ ይሆናል። የተጠቂዎች ቁጥር በግምት አንድ ሚሊየን ሊደርስ ይችላል። በሌሎች ሀገራት በኤች.አይ.ቪ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ሆኖ የሕዝብ ቁጥራቸው አነስተኛ ከሆነ

21

በኤች.አይ.ቪ የተያዙት ሰዎች ቁጥር ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ሆኖ ሊታይ ይችላል። በሌሎቹ ሀገራት የኤች.አይ.ቪ ስርጭት ከኢትዮጵያ ያነሰ ቢሆንም የተጠቃው ሕዝብ ቁጥር ሰፊ ስለሚሆን ከኤች.አይ.ቪ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ቁጥርም እንዲሁ ትልቅ ይሆናል።

ኤች.አይ.ቪ በኢትዮጵያ ሁለት በመቶ የመሰራጨቱን ሁኔታ ከሀገሪቱ ሁኔታ አንጻር ልንረዳው ይገባል። በከተማዎች ውስጥ ያለው ስርጭት ከገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል አንጻር ሲታይ ከፍተኛ ነው። የተወሰኑ የተጋላጭ ሰዎች እድሜያቸው ከ15- 45 የሚሆኑት ከፍተኛውን የኤች.አይ.ቪ ስርጭት መጠን ይወስዳሉ። በኢትዮጵያ ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍበት ዋነኛው መንገድ ከተቃራኒ ጾታ ጋር የሚደረግ ወሲባዊ ግንኙነት ነው። ይህ ቫይረስ የሚተላለፈው በወሲብ ጊዜ በሚመነጩ ፈሳሾች ንክኪ፣ በደም እና በእናት ጡት ወተት አማካይነት ነው። ልዩ ልዩ ድርጊቶች እነዚህን ፈሳሾች ከሰው ወደ ሰው እንዲተላለፉ ሊያደርጉ ይችላሉ። እነዚህን የመተላለፊያ መንገዶችን በአግባቡ መረዳት አድልዎና መገለልን እንዲሁም አለመቀበልን ለማስቆም ይጠቅማል። ኤች.አይ.ቪ በዓይነ ምድር፣ በምራቅ፣ ላብ፣ ዕንባ ወይም በሽንት አማካይነት አይተላለፍም።

አድልዎ ማኅበራዊ አለመቀባበልን በሚያስከትል መልኩ ሰዎችን በተለያየ መንገድ የሚከፋፍል አካሄድ ነው። ስለዚህ ሰዎች ማኅበራዊ ተቀባይነትን ከማጣታቸው የተነሳ ሊገለሉ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ አድልዎ ትክክለኛ ካልሆነ ከፍርሀት ሊመነጭ ይችላል። ለምሳሌ፦ ሰዎች ኤች.አይ.ቪ እንዳይዛቸው ከመፍራት የተነሳ ኤች.አይ.ቪ በደሙ ከሚገኝ ሰውጋር በአንድ ክፍል ውስጥ አብሮ መቀመጥ ወይም መገልገያዎችን

22

23

መጋራት አይፈልጉም። ሆኖም ይህ ፍርሀት በእውነታ ላይ የተመሠረተ አይደለም። ኤች.አይ.ቪ ከላይ የተገለጹትን ድርጊቶች በመፈጸም አይተላለፍም። ኤች.አይ.ቪ እና ኤድስ ምን እንደ ሆኑ እና ቫይረሱ እንዴት እንደሚሠራጭ መረዳት አድልዎና መገለልን እና አለመቀበልን ለማስቆም የመጀመሪያዎቹ ሂደቶች ናቸው።

ከአድልዎ በተጨማሪ አንዳንዶች ኤች.አይ.ቪ መኖሩን ፣ የሚያስከትለውን ጉዳት እንዲሁም አቅሙን እንደ ሌለ ቆጥረው ሊክዱ ይችላሉ። ይህም በተለያየ መንገድ ሊገለጽ የሚችል ሲሆን፣ እያንዳንዱ መገለጫ የተዛባ መረዳትን እና አመለካከትን በመፍጠር በሽታውን የመከላከል እና ሕክምና የማግኘቱን መንገድ ሊያደናቅፍ ይችላል። ለምሳሌ፦አንድ ሰው ኤች.አይ.ቪ እና ኤድስ የሚባል ነገር አለመኖሩን ሲያምን፣ ሌላኛው ሰው ደግሞ ቫይረሱ የሚያስከትለው ጉዳት እንደ ሌለ ቆጥሮ ተገቢውን የህክምና እርዳታ ከማግኘት ሊቆጠብ ይችላል። ሦስተኛ ሰው ደግሞ ቫይረሱ በግለሰብ እንዲሁም በማኅበረሰብ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ሊክድ ይችላል። እነዚህ አስተሳሰቦች እያንዳንዳቸው ሰዎች ኤች.አይ.ቪ በደማቸው ውስጥ መኖሩን እና አለመኖሩን አውቀው የመከላከያ መንገዶችን እንዳይጠቀሙ እንዲሁም የሕክምና እርዳታ እንዳያገኙ ያደርጓቸዋል።

24

ለ) መልዕክት

ነባራዊ ሁኔታን መካድ፣ አድልዎ እና መገለል የሚመነጩት ከአስተሳሰብ እና ከአመለካከት ነው። እነዚህ ድርጊቶች አብዛኛውን ጊዜ በሰው ላይ መፍረድን የሚያካትቱ ሲሆን ሁኔታውን ሙሉ በሙሉ ለመረዳት በሚያስፈልገው መረጃ ላይ የተደገፉ አይደሉም። በክርስቶስ የምናምን እንደ መሆናችን መጠን በሰው ላይ ከመፍረድ ተቆጥበን እና ጥላቻን አስወግደን በፍቅር ልንተሳሰር ይገባል። ይህም ከአስተሳሰባችን ይጀምር እና በድርጊቶቻችን አማካይነት ይገለጻል። ምክንያቱም የሰው እምነቱ የሚታወቀው በእምነቱ መሠረት በሚሰራው መልካም ሥራ ነውና ነው፡፡ ስለዚህ ነው ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ “ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው” (ያዕ. 2፥17) በማለት የተራበን ማብላት፣ የታመመን መጠየቅ፣ የተጨነቀን ማጽናናት እና ማበረታታት፣ የተቸገረን መርዳት እንዳለብን ያስተማረን፡፡

በኤች.አይ.ቪ እና በኤድስ ዙሪያ የሚታዩ እና የሚደረጉ አድልዎና መገለል እና አለመቀበል በኅብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከማስከተላቸውም በተጨማሪ በክርስቶስ ለሚያምን ሕዝብ ትልቅ ኃጢአት ነው። ድጋፍ እና ክብካቤ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ተገቢውን ድጋፍና እንክብካቤ ባለማግኘታቸው በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳሉ። ሰዎች ስለ ጉዳዩ መነጋገርን በፈሩ ቁጥር፣ ኅብረተሰቡ ባገለላቸው እና መድልዎ በፈጸመባቸው ቁጥር ማኅበረሰባቸውን ይጎዳሉ። ስለሆነም ሰዎች ስለ ኤች.አይ.ቪ እና ኤድስ የመረዳት ዕድል እንዳይኖራቸው ወደ ኋላ ያሰኟቸዋል። ምክንያቱም በሌሎች ላይ ሲፈጸም ያዩት መገለል እና መድልዎ በእነርሱም ላይ እንዳይደርስ ስለሚሰጉ ከጋብቻ በፊት የሚደረግ የኤች.አይ.ቪ ምርመራን

25

እንዳያከናውኑ እና ቫይረሱ በደማቸው መኖሩን ወይም አለመኖሩን እንዳያረጋግጡ እንቅፋት ይሆናቸዋል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ - ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚያደርጉ መንገዶችን ጨምሮ - ሕክምና የማግኘትን ዕድልም ይዘጋሉ። ሆኖም የሃይማኖት መሪዎች ይህንን በመለወጥ እና አድልዎ እና መገለልን በመግታት፣ ሰዎች በሰዎች ላይ እንዳይፈርዱ መረዳትን በመፍጠር እና በሚያደርጉት ሁሉ የጌታችን እና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር ለማኅበረሰቡ በማሳየት ወሳኝ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል።

26

1. እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት።(ዮሐንስ 15፥12)

2. ሰውን ሁሉ እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ (ማቴዎስ 22፥39)

3. ፍቅር ያስታግሣል፥ ፍቅር ያስተሳዝናል፣ ፍቅር አያቀናናም፣ ፍቅር አያስመካም፣ ፍቅር አያስታብይም፣ ብቻዬን ይድላኝ አያሰኝም፤ አያበሳጭም ክፉ ነገርን አያስብም ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለአመጻ ደስ አይለውም፣ ሁሉን ይታገሳል ሁሉን ያምናል ሁሉን ተስፋ ያደርጋል በሁሉ ይጸናል፡፡(1 ቆሮንቶስ 13፥ 4-8)

4. እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፥ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል። (ማቴዎስ 7፥ 1-2)

5. በብርሃን አለሁ የሚል ወንድሙንም የሚጠላ እስከ አሁን በጨለማ አለ። ወንድሙንም የሚወድ በብርሃን ይኖራል ማሰናከያም የለበትም፡፡ (1 ዮሐንስ 2፥ 9-10)

6. እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለ ሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን

ሐ) መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች

27

እናውቃለን፤ ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል። ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ። (1 ዮሐንስ 3፥ 14-15)

7. ወዳጆች ሆይ፥ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ የሚወደውም ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደ እግዚአብሔርንም ስለሚያውቅ፥ እርስ በርሳችን እንዋደድ። (1 ዮሐንስ 4፥7)

8. ማንም እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል? እግዚአብሔርንም የሚወድ ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትእዛዝ ከእርሱ አለችን። (1 ዮሐንስ 4፡20-21)

9. አንድ ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ ከከተማዎችም በአንዲቱ ሳለ፥ እነሆ፥ ለምጽ የሞላበት ሰው ነበረ፤ ኢየሱስንም አይቶ በፊቱ ወደቀና። ጌታ ሆይ፥ ብትወድስ፥ ልታነጻኝ ትችላለህ ብሎ ለመነው። እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና። እወዳለሁ፥ ንጻ አለው፤ ወዲያውም ለምጹ ለቀቀው። (ሉቃስ 5፥ 12-13)

10. ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል። እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። ተርቤ አብልታችሁኛልና፤ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፤ እንግዳ ሆኜ

28

ተቀብላችሁኛልና፤ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፤ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፤ ታስሬ ጎብኝታችሁኛልና።. . . ንጉሡም መልሶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል:: (ማቴዎስ 25፥34-36፣ 40)

11. አንድ ሳምራዊ ግን በዚያ በኩል ሲያልፍ ወደ ሰውየው መጣ፤ ባየውም ጊዜ ራራለት፤ ወደ እርሱም ቀርቦ ዘይት እና የወይን ጠጅ በቁስሉ ላይ አፈሰሰ፤ በጨርቅም ጠምጥሞ አሠረለት፤ ከዚያም በኋላ በገዛ ራሱ አህያ ላይ አስቀምጦት ወደ አንድ የእንግዶች ማደሪያ ቤት ወሰደው፤ በዚያም በልዩ ጥንቃቄ ተንከባከበው (ሉቃስ 10፥33-34)

12. ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰ። የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው እንጂ እርሱ ወይም ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም። (ዮሐንስ 9፥3)

13. ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው እግዚአብሔር በክፉ ቀን ያድነዋል። (መዝሙር 41፥1)

14. በልዩ ልዩ ደዌም የታመሙትን ብዙዎችን ፈወሰ፥ ብዙዎችንም አጋንንት አወጣ፥ . . . (ማርቆስ 1፥34)

29

ርዕስ: “ወንድሙንም የሚወድ በብርሃን ይኖራል”

አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ እሱ እኛን በወደደን መውደድ እርስ በእርሳችን እንድንዋደድ አስገንዝቦናል። ክርስቲያን በሙሉ ይህንን መልዕክት ሊተገብረው እና የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ የጥሪው ዋነኛ አካል ሊያደርገው ይገባል። ስለ ፍቅር፣ እርስ በርስ ስለመዋደድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በልዩ ልዩ መልኩ ተገልጿል። ባልንጀሮቻችሁን እንደ ራሳችሁ አድርጋችሁ ውደዱ። ለራሳችሁ እንዲሆንላችሁ የምትመኙትን ለሌሎችም ተመኙ። ስለፍቅር መልዕክት ሙሉ በሙሉ ለመረዳት የፍቅርን ትርጓሜ ከቃለ-እግዚአብሔር ላይ እንመልከት፦

“ፍቅር ያስታግሣል፥ ፍቅር ያስተሳዝናል፣ ፍቅር አያቀናናም፣ ፍቅር አያስመካም፣ ፍቅር አያስታብይም፣ ብቻዬን ይድላኝ አያሰኝም፤ አያበሳጭም ክፉ ነገርን አያስብም ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለአመጻ ደስ አይለውም፣ ሁሉን ይታገሳል ሁሉን ያምናል ሁሉን ተስፋ ያደርጋል በሁሉ ይጸናል፡፡” (1 ቆሮንቶስ 13፥ 4-8) ፍቅራችንን ለሌሎች በተግባራችን ከመግለጻችን ባሻገርም በሌሎች ላይ ከመፍረድ መቆጠብ ይኖርብናል። በእናንተ ላይ እንዳይፈረድባችሁ በማንም ሰው ላይ አትፍረዱ፤ ምክንያቱም በሌሎች ላይ በምትፈርዱበት ዐይነት

መ)ዐውዳዊ ስብከት

30

በእናንተም ላይ ይፈረድባችኋል፤ እንዲሁም በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል። አድልዎና መገለልን ለማስወገድ በሌሎች ላይ ከመፍረድ መቆጠብ አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ከአድልዎና መገለል ጀርባ የሚገኘው በሌሎች ላይ መፍረድ ነው። ነገር ግን፣ የእግዚአብሔር ቃል የሚነግረን እና የሚያበረታታን በሌሎች ላይ ከመፍረድ እንድንቆጠብ ብቻ ሳይሆን ልክ እኛ እንዲፈረድልን በምንፈልግበት መልኩ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝባቸውን ወገኖች እየደረሰባቸው ያለውን መገለል እና መድልዎ እንዳይደርስባቸው እኛ አርአያ በመሆን ፍቅርና ርህራሄን በማሳየት ልንንከባከባቸው ይገባል፡፡

ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስታመነዝር አገኘናት ብለው ወደርሱ እንዲፈርድባት፣ እንድትገለል ያመጡአትን ሴት ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት ሰው አስቀድሞ ይውገራት በማለት ጎንበስ ብሎ በምድር ላይ በጣቱ በጻፈ ጊዜ ያንዱ ኃጢአት በሌላው ግንባር ላይ ተጽፎ በማየታቸው ሁሉም ትተው ተበትነዋል፡፡ ክርስቶስም ቀና ብሎ ከሴቲቱ በቀር ማንንም ባላየ ጊዜ አንቺ ሴት እነዚያ ከሳሾችሽ የታሉ አላት እርስዋም ጌታ ሆይ አንድስ እንኳ አለች፣ ኢየሱስም እኔም አልፈርድብሽም ሂጂ በይ ካሁን ጀምሮ ኃጢአት አታድርጊ በማለት በፍቅር አሰናብቷታል፡፡ (ዮሐ 8፥10-11) ጥላቻን በማስወገድ ለችግር የተጋለጡ ሰዎችን ድጋፍና እንክብካቤ ማድረግና አለሁላችሁ ባይነት እንደ ክርስቶስ ማሳየት ይገባል:: ጥላቻ ከነፍሰ ገዳይነ እና ከእምነተ ቢስነት እንደሚመነጭ፤ የእግዚአብሔር ጥሪም አንዳችን ሌላችንን

31

32

እንዳንጠላ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው በግልፅ የሚናገሩ ክፍሎችን በመጽሐፍ ቅዱስ እናነብባለን። በአንጻሩ የተጠራነው በፍቅር ኅብረት ለማድረግ ነው። ልበ አምላክ ዳዊት በመዝሙር 133፥ 1 ላይ ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ እነሆ መልካም ነው እነሆም ያማረ ነው እንዳለ የተጠራንበትን የፍቅር ጥሪ እያሰብን በመተዛዘን፣ በመረዳዳት እና በፍቅር በዚህች ዓለም ላይ በተፈቀደልን እድሜ መጠን ልንኖር ይገባናል፡፡ በአስተሳሰባችን እና በፍርዳችን ባልተገደበ መልኩ ለሁሉ ፍቅርን ማሳየት አለብን። ለታመሙ እና ችግር ለገጠማቸው ሰዎች ፍቅርን ማሳየት አቅም በፈቀደ መጠን ድጋፍና እንክብካቤ ማድረግ አለብን። ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅርን እንዳሳየን መጠን እኛም ለተቸገሩና ላዘኑ ለተከዙ ወገኖቻችን ፍቅርን ልናሳይ ይገባል።

ከዚህም ጋር በዝሙት ወይም በደም ንክኪ ምክንያት ለበሽታው የተጋለጡትን ሰዎች ማግለል እና አድልዎ ማድረግ፣ የፍቅር እና የርህራሄ ተግባርን መንፈግ ሌላው ለአንተ ሊደረግልህ የምትፈልገውን አንተም ለሌላው አድርግለት የሚለውን አምላካዊ ቃል የሚሽር ስለሆነ የችግሩን ስፋት እና ጉዳት ለኅብረተሰቡ ማስተማር የካህናት ሃላፊነት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ላይ በተግባር እንደተገለጠ እኛም ስለሰው ያለን ፍቅር ኤችአይቪ በደማቸው ለሚገኝ ወገኖች በምናደርገው እንክብካቤ መገለጽ ይኖርበታል፡፡

33

፫. ኤች.አይ.ቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ መከላከል

ሀ) ዐውድ

ኤች.አይ.ቪ የሚሰራጭበት አንደኛው መንገድ ቫይረሱ በደሟ ከሚገኝ እናት ወደ ልጅ መተላለፍ ነው። ኤች.አይ.ቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚያስችል ህክምና በሀገራችን በሁሉም ቦታ እና ሥፍራ በነጻ የሚገኝ አገልግሎት ነው ይህንንም የህክምና አገልግሎት በነጻ እና በአግባቡ በመከታተል ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ መከላከል ይቻላል።

አንዲት እናት ቫይረሱ በደሟ የሚገኝ ከሆነች ቫይረሱ ወደ ጸነሰችው ልጅ ሊተላለፍ የሚችልበት ዕድል የሰፋ ነው። ይህንን ስርጭት አንዲት እናት ለመጽነስ ከመወሰኗ በፊት በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የኤች.አይ.ቪ ምርመራ ማድረግ ይኖርባታል። ይህም ለህጻኑም ሆነ ለእርሷ ተገቢውን የህክምና ክትትል እንድታደርግ እና ጤንነታቸውን ለመጠበቅ ያስችላታል፡፡ ዛሬ ዛሬ ኤች.አይ.ቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚያደርጉ የሕክምና አማራጮች ቢኖሩም ሰዎች ሊጠቀሟቸው

34

35

እንደሚገባ ካላወቁ ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት ወደ ማግኘት አይመጡም። ይህ በተለይም አስፈላጊ የሚሆነው ብዙ እናቶች ያለ ሕክምና ባለሙያ እገዛ በጤና ተቋማት ሳይሆን በመንደር አዋላጆች በየቤታቸው ስለሚወልዱ ነው። ይህ በሚሆንበት ጊዜ የኤች.አይ.ቪ ምርመራ የሚያደርጉበት ዕድል የጠበበ ነው። ከዚህም የተነሳ ሕክምናው አስፈላጊ ሆኖ ቢገኝ እንኳን አይጠቀሙበትም።

የኤች.አይ.ቪ ምርመራን በመላው ኢትዮጵያ በነጻ ማግኘት የሚቻል ሲሆን ነፍሰጡር እናቶች በማንኛውም ጊዜ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ የህክምና አገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ። ከዚህ ምርመራ በተጨማሪም በእርግዝና ወቅት እና ከወሊድ በኋላ ስለአለው የአመጋገብ ሥርዓት እና ጤናማ እርግዝናን በተመለከተ ተገቢውን የምክክር አገልግሎት በጤና ተቋማት ማግኘት ይችላሉ ።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ 15,000 የሚያህሉ ልጆች ከኤች.አይ.ቪ ጋር ተወልደዋል። (FHAPCO 2010) አብዛኞቹ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ እናቶች የኤች.አይ.ቪን ከእናት ወደ ልጅ ሥርጭት የሚገቱ የመንግሥት አገልግሎቶችን የመጠቀም ዕድሉ ቢኖራቸውም አልተጠቀሙበትም። ልምድ ካላቸው የሕክምና ባለሙያዎች ጋር በመነጋገር በእነዚህ መርሀ-ግብሮች ውስጥ የተቻለውን ያህል ህጻናት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና ነፍሰጡር እናቶችን የሕክምና ድጋፍ እንዲያገኙ ማበረታታት አስፈላጊ ነው። ይህንን ማድረግ እናቲቱን እና ልጆችን በብዙ መንገድ ያግዛል፣ ቫይረሱ በደሟ የሚገኝባት እናት አስፈላጊውን ህክምና በወቅቱ እንድታገኝ እና ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን እንድትከተል፣ ከቫይረሱ ነጻ የሆነ እና ጤናማ ልጅ እንድትወልድ ተገቢውን የህክምና ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እናቶች ተገቢውን የህክምና

36

አገልግሎት በማድረጋቸው ጤናማና ረዥም ሕይወት እንዲኖራቸው ከማስቻሉም በተጨማሪ የሚወልዷቸው ልጆችም ከኤች.አይ.ቪ ነጻ ሆነው የመወለድ ዕድላቸው የሰፋ ይሆናል።

የሃይማኖት ተቋማት እና የሃይማኖት መሪዎች ከሥራቸው ጋር ሊያቀናጇቸው ከሚገቡ ዐበይት ጉዳዮች አንዱ ሴቶች የሕክምና ተቋማት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማበረታታት ነው። ይህም ኤች.አይ.ቪን መከላከል እና አስፈላጊውን ሕክምና ማግኘትን የሚያጠቃልል ሲሆን የእናቶችን እና ህጻናትን ጤና እና ደህንነት ያካትታል።

ነፍሰጡሯ እናት ቫይረሱ በደሟ የሚገኝ ከሆነ ሌሎች የሕክምና አማራጮችን ታገኛለች። እነዚህ ሕክምናዎች ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚረዱ ሲሆኑ እናቲቱም ረዥም እና ጤናማ ሕይወት እንድትኖር ያግዟታል። ከሕክምናው በተጨማሪም የሕክምና ባለሙያዎች ለመውለድ ሂደቱ የሚጠቅሙ እና የቫይረሱን ወደ ፅንሱ የመተላለፍ ዕድል በእጅጉ የሚቀንሱ ልዩ ልዩ ዓይነት ድጋፎች ያደርጉላታል። ለነፍሰጡር እናቶች ልንሰጥ የሚገባን አስፈላጊ ምክር በሕክምና ባለሙያዎች የሚረዱበትን ዕድል እንዲጠቀሙ ማሳሰብ ነው።

37

38

ለ) መልዕክት

በመጀመሪያ፣ በሌሎች ላይ ከመፍረድ መቆጠብ አለብን። ባሎች አስቸጋሪ ሁኔታ በተፈጠረ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ወቅት እና ጊዜያት ሁሉ የሚስቶቻቸው ደጋፊዎች ሆነው ሊቆሙ ይገባል። በመጨረሻም፣ ልጆቻችንን ልንከባከብ እና ልናከብር የምንችልበት አንደኛው እና ዋነኛው ኤች.አይ.ቪ በደማችን ውስጥ መኖር እና አለመኖሩን በማወቅ እና ቫይረሱ በደም ውስጥ ቢገኝ እንኳ ከእናት ወደ ጽንሱ እንዳይተላለፍ ተገቢውን የሕክምና ክትትል በማድረግ ጤናማና ጠንካራ ልጅ እንዲኖረን በማድረግ ነው፡፡

39

1. በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፥ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ። (ኤርምያስ 1፥5)

2. አባቴና እናቴ ትተውኛልና፥ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ። (መዝሙር 27፥ 10)

3. ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት (ማቴዎስ 2፥11)

4. ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ ለየኝ በጸጋውም ጠራኝ (ገላትያ 1፥15)

ሐ) መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች

40

መ)ዐውዳዊ ስብከት

ርእስ: አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቆሮንቶስ መልእክቱ ከክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መምጣት በኋላ በሐዲስ ተፈጥሮ ሁሉም አዲስ ፍጥረት ሁኗል አሮጌው ነገር አልፎአል እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኖአል (2ቆሮ 5፥17) በማለት ስለ አዲስ ሕይወት፣ ስለ ብሩህ ተስፋ በስፋት ይነግረናል፡፡ አዲስ ሕይወት ያለው በጨለማ እንኖር የነበርን፣ በፍርሀት ተውጠን የነበርን በአዲስ ተፈጥሮ በአዲስ ጥምቀት የመንግሥቱ ወራሾች ለመሆን የበቃን የተዘጋጀን መሆናችንን የሚያሳይ ነው፡፡

ዛሬም እናቶች የጊዜው ፈተና የሆነውን ኤች.አይ.ቪ ከእነሱ ወደ ልጃቸው እንዳይተላለፍ ከመውለዳቸው በፊት አስፈላጊውን ሁሉ የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆን ጤናማና ደስተኛ ልጅ እንዲወልዱ ተገቢውን የምክር አገልግሎት በጤና ተቋማት በመሄድ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡

ዛሬ በኢትዮጵያ ኤች.አይ.ቪ በደማቸው የሚገኝባቸው ሰዎች ከባድ ፈተና ይገጥማቸዋል፣ እንዲሁም ሰዎች ስለ እነርሱ አሉታዊ መላ ምቶችን ይደረድራሉ። እግዚአብሔር እርስ በእርስ እንድንዋደድ እና አንዳችን በሌላችን ላይ እንዳንፈርድ ያዘዘን በመተግበር አርአያ ልንሆን ያስፈልጋል።

41

ኤች.አይ.ቪ ከእናት ወደ ፅንሱ ሊተላለፍ የሚችልበት ዕድል በጣም ሰፊ ነው፣ ነገር ግን ይህንን በብዙ መጠን ልንከላከል እንችላለን። ይህንን ለማድረግ በመጀመሪያ በደማችን ውስጥ ቫይረሱ የመገኘቱን ወይም ያለ መገኘቱን ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ቫይረሱ በደማችን ከተገኘ ተገቢውን የህክምና ክትትል በማድረግ ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚያስችለውን ህክምና በማግኘት ጤናማ ልጅ መውለድ እንችላለን፡፡ ተገቢውን የህክምና ክትትል አድርገን ሁኔታዎቹ በእርግጥም ተለዋውጠው ቢገኙም ለልጆቻችን ፍቅር እና ርህራሄን ከማሳየት እና እነርሱን ለመንከባከብ የቻልነውን ሁሉ በማድረግ ለልጆቻችን ያለንን ፍቅር በድርጊታችን ሁሉ ማሳየታችን ግን ፈፅሞ አይለወጥም። ምክንያቱም ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸውና፡፡

42

፬. ጾታዊ ጥቃት

ሀ) ዐውድ

ጾታዊ ጥቃት ልዩ ልዩ ገፅታ ሊኖረው ይችላል፡፡ ከጾታዊ ጥቃት መካከል በአብዛኛው የሚታየው የሴቶች ጥቃት ነው ። በኢትዮጵያ የሴቶች ጥቃት የሚከተሉትን ያጠቃልላል፦ ሰባ አምስት በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ተገርዘዋል፣ ይህም የተፈፀመው የጤናን ሁኔታ ባላገናዘበ መልኩ ነው፤ ስምንት በመቶ የሚሆኑት ሰዎች ያገቡት ተጠልፈው ነው፣ ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ወላጆቻቸው እነርሱን የመደብደብ መብት እንዳላቸው ይሰማቸዋል፣ ወደ አምሳ በመቶ የሚጠጉት ሴቶች በሕይወታቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ በቤተሰባቸው አባላት ወሲባዊ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል፣ እንዲሁም አያሌ ልጃገረዶች በግዴታ እንዲያገቡ ይደረጋሉ።

የሴቶች ጥቃት ዘርፈ ብዙ ጉዳቶችን ያስከትላል። በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች ሴትነታቸውን ተመርኩዞ የሚቃጡባቸው በማኅበራዊም ይሁን በግል ሕይወት ውስጥ የሚፈጸሙ አካላዊ፣ ወሲባዊ ወይም ስነ-ልቡናዊ ጉዳት የሚያስከትሉ

43

ተግባራት ናቸው፡፡ ሴቶች በሚደርስባቸው ጥቃት ሳቢያ ከሰው ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት መልካም እንዳይሆን ከማድረጉም በተጨማሪ ሊኖራቸው የሚገባ በራስ የመተማመን ክህሎታቸውን እንዲያጡ ያደርጋቸዋል፡፡ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ድብርትን፣ ቁጣን፣ አደገኛ እና ያልተለመደ ጠባይ ማሳየትን፣ ሰውነትን የሚመርዙ ነገሮችን መጠቀምን፣ ለኤች.አይ.ቪ እና ለተላላፊ በሽታዎች መጋለጥ፣ ማኅበራዊ አድልዎን፣ በሚደርስባቸው ጥቃት የተነሳ ለከፍተኛ ሕክምና ወጪ መዳረግ እንዲሁም የሥራ ገበታቸውን እስከማጣት ድረስ ሊያስከትል ይችላል። የሴቶች ጥቃት በተጨማሪም ሕፃናትን ይጎዳል። ጥቃት የሚደርስባቸው ወይም ጥቃት ሲፈጸም የሚመለከቱ ህፃናት ከአካላዊ፣ ስነ-ልቡናዊ እንዲሁም ከማኅበራዊ ጤና አንጻር እክል ሊገጥማቸው ይችላል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን የሚቃወሙ ማለትም የሴት ልጅ ብልት ትልተላ፣ በቤት ውስጥ የሚደርስ ጭቆና፣ ጠለፋ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ያለድሜ ጋብቻ እና የመሳሰሉት በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ውስጥ ተካተው በግልጽ ተቀምጠዋል። (ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ (2005) አንቀጽ፡ 564፣565፣587፣620 እና 648) ሆኖም አብዛኛው ጥቃት የሚከሰተው በቤት ውስጥ ስለ ሆነ ጥቃት መፈጸሙን ማወቅ ያዳግታል። ሴቶች ጥበቃ ማግኘት አስፈልጓቸው ጥቃት እንደ ተፈጸመባቸው እንዳያሳውቁ የሚያደርጉ በጉዳዩ ላይ የሚደርሱ ማኅበራዊ መድልዎ፣ ጉዳያቸውን በአግባቡ ለማመልከት የሚቻልባቸው አመቺ አማራጮች ማጣት እንዲሁም ከሌሎች ሴቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ማጣት የመሳሰሉ ጉዳዮች ሊገቷቸው ይችላሉ።

44

45

ለ) መልዕክት

በመላው ኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት እና የሃይማኖት መሪዎች በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለመከላከል እና ለማስቆም ከፍተኛ ሚና መጫወት ይችላሉ። በመጀመሪያና በዋነኛነት የሴቶች ጥቃት ምን ማለት እንደ ሆነ መረዳት የሚያስፈልግ ሲሆን በዚህ ርዕስ ላይ ለመወያየት የሚቻልበት አመቺ ጊዜና ቦታ ማዘጋጀትም ይኖርብናል። ለምሳሌ፦ ሰዎች የግል ጉዳያቸውን በአደባባይ ለውይይት ማቅረብ አይፈልጉም፣ ደግሞም ይህንን ውይይት - የሃይማኖት አባት ቢሆን እንኳ - ተቃራኒ ጾታ ባለበት ማድረጉ ምቾት አይሰጣቸውም። ስለዚህ ሴቶቹ ግላዊ ጉዳዮቻቸውን በነጻነት መወያየት እንዲችሉ ተገቢውን አገልግሎት ማመቻቸታችን ላይ እርግጠኛ መሆን ይኖርብናል። ምናልባትም ሴቶችን ብቻ ልናገኝባቸው የምንችልበትን መንገድ መፍጠር ያስፈልጋል ለምሳሌ በሰንበት ትምህርት ቤቶች እና ወርኀዊ ፕሮግራም ለሴቶች ንስሓ ልጆች ብቻ በማዘጋጀት፡፡ በተጨማሪም የሃይማኖት መሪዎች ጥቃትን በሚቋቋሙበት እና በሚያስወግዱበት መንገድ ላይ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ክህሎት ማዳበር ይኖርባቸዋል።

ሌላው በታዳጊ እና በወጣት ሴቶች ላይ የሚደርሰው ጾታዊ ጥቃት ነው፡፡ ይህም የሴት ልጅ ብልት ትልተላ፣ ወሲባዊ ጥቃት፣ ጠለፋ፣ ያለእድሜ ጋብቻ እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እነዚህ ጥቃቶች በታዳጊ እና በወጣት ሴቶች የወደፊት ሕይወት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡ ስለሆነም በልጆቻችን ላይ የሚደርሰውን አሉታዊ ተጽእኖ በአግባቡ በመረዳት ልንከላከልላቸው እና ልንጠብቃቸው ይገባል፡፡

46

መጽሐፍ ቅዱስን መመሪያቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስንም ተምሳሌታቸው አድርገው በመጠቀም የሃይማኖት መሪዎች በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም በቂ መልዕክት ማስተላለፍ ይችላሉ። በክርስቶስ ፍቅር በመመራት የሃይማኖት አባቶች ኀብረተሰቡ የትዳርን ክቡርነት እና በትዳር ውስጥ ሊኖር ስለሚገባው ጤናማ ግንኙነት፣ ፍቅር፣ እርስ በርስ መዋደድ እና መቻቻልን መረዳታቸውን ማረጋገጥ ይችላሉ።

47

1. በእኔና በአንተ መካከል፥ ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል የምትጠብቁት ቃል ኪዳኔ ይህ ነው ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ። (ዘፍጥረት 17፥ 10)

2. እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና። (ማቴዎስ 7፥12)

3. ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፥ እንደዚሁም ደግሞ ሚስቲቱ ለባልዋ። (1 ቆሮንቶስ 7፥3)

4. አንድም የአካል ክፍል ቢሣቀይ ሌሎች የአካል ክፍሎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ የአካል ክፍልም ቢከበር ሌሎች የአካል ክፍሎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 12፥ 26)

5. ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና። (ገላትያ 3፥ 28)

6. ባሎች ሆይ! ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደወደደና ራሱን ስለ እርስዋ አሳልፎ እንደ ሰጠ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ:: (ኤፌሶን 5፥ 25)

ሐ) መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች

48

7. እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ (ኤፌሶን 5፥ 28)

8. ሚስቶች ሆይ፥ በጌታ እንደሚገባ ለባሎቻችሁ ተገዙ። ባሎች ሆይ፥ ሚስቶቻችሁን ውደዱ መራራም አትሁኑባቸው:: (ቆላስይስ 3፥ 18-19)

9. እንዲሁም፥ እናንተ ባሎች ሆይ፥ ደካማ ፍጥረት ስለ ሆኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ፤ ጸሎታችሁ እንዳይከለከል አብረው ደግሞ የሕይወትን ጸጋ እንደሚወርሱ አድርጋችሁ አክብሩአቸው።

(1 ጴጥሮስ 3፥7)

49

መ)ዐውዳዊ ስብከት

ርዕስ: ፍቅር

የፍቅር አይነቱ ብዙ ሲሆን የቤተሰብ ፍቅር፣ የሀገር ፍቅር፣ የጓደኛ ፍቅር፣ የልጆች ፍቅር እያልን ልንገልጻቸው እንችላለን፡፡ የቤተሰብ ፍቅር ስንል ከባልና ሚስት ጀምሮ በጠቅላላው የቤተሰቡ አባላት ፍቅር ማለት ነው፡፡ በዚህ ቤተሰብ ውስጥ ደግሞ ወንድ እና ሴት ጾታዎች ይገኛሉ፡፡ በሰዎች መካከል ሊኖር የሚገባውን ተገቢ ግንኙነት መረዳትን በተመለከተ እግዚአብሔር የሚናገረውን ለመረዳት አንድ እና ሁለት ጥቅሶችን ብቻ ገረፍ ገረፍ አድርጎ ማንበብ ለተዛባ መረዳት ይዳርጋል። “ሚስቶች ሆይ ለባሎቻችሁ ተገዙ” (ቆላስይስ 3፥ 18-19) እንደሚለው ያሉ ጥቅሶችን በትክክል አለመረዳት በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አማካኝነት የተላለፉልንን የእግዚአብሔርን ቃል ወደሚቃወሙ ድርጊቶች ይመራናል። በማኅበረሰባችን መካከል የሚገኙ የቤተሰብ አባላት በእግዚአብሔር ቃል ላይ ተመሥርተው የጤናማ ግንኙነትን ተፈጥሮ መረዳታቸውን እና በእርስ በእርስ ግንኙነታቸው ላይ ሊጎዷቸው የሚችሉ ሁኔታዎችን ለማስወገድ እና ለመከላከል እንዲችሉ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ አለብን።

50

አንዳንዶቹ ጥቃት የሚደርስባቸው በሚወዷቸው የቤተሰብ አባላት አማካይነት ነው። እንዲህ ያሉት ድርጊቶች በኢትዮጵያ የሚፈጸሙ ሲሆን እንዲለወጡ የተቻለንን ልናደርግ ይገባል።

ክርስቶስን እንደሚከተል ማኅበረሰብ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ መመሪያችን፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ደግሞ እንደ ምሳሌያችን በመጠቀም ያለንን መረዳት እያነጽን ወደ ፊት ልንገሰግስ ይገባል።

ቃለ-እግዚአብሔርን መሠረት ያደረጉ እሴቶችን እንድናዳብር ከሚረዱን ዋነኛ መልዕክቶች አንዱ ʻለራሳችሁ እንዲደረግላችሁ የምትፈልጉትን ለሌሎች አድርጉʼ የሚለው ወርቃማው ሕግ ነው። ስለዚህ መተሳሰብን ልናበረታታ ይገባል። ይህንን በማድረጋችንም አንዱ ሰው ሌላኛውን ማጥቃቱ እግዚአብሔር የሰው ዘር እንዲያስወግደው የጠራን ነገር እንደሆነ እናሳያለን። መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉንም ሰዎች ስለ መረዳት፣ ማቅረብ፣ መከራን መካፈል እንዲሁም ስለ ማክበር ይናገራል። በዚህ ጊዜ በክርስቶስ አንድ ከመሆናችን የተነሳ ሌሎችን ስለ መውደድ እና ለሌሎች መልካምን ስለመመኘት እንጂ ስለ መከፋፈል አይሆንም።

ጋብቻ ቅዱስ ነው። ይህ መተሳሰር በእግዚአብሔር ጥሪ ላይ እንደ ተመሠረተ መግለጥ የሚቻለው በመከባበር፣ ደግነት እና ርህራሄ ላይ ሲቆም ነው። በተጨማሪም በፍቅር እና በመረዳት ላይ የተመሠረተና አንዳችን ከሌላችን

51

ጋር ለሚኖረን ግንኙነት የኢየሱስ ክርስቶስን ድንቅ ተምሳሌትነት የምንሻበት ጉዳይ ነው። ልክ በሰው ዘር ላይ የሚደርሰውን መከራ በምንመለከትበት ዓይን እግዚአብሔር የትዳር አጋራችንን ፍቅር ልናየው እንደምንናፍቀው ፍቅር አድርገን እንድናየው ይጠራናል። በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ባሎች ሚስቶቻቸውን እንደገዛ አካላቸው አድርገው ሊወድዱ እንደሚገባ እናነብባለን። በተጨማሪም ጋብቻ ሃይማኖታዊ ስምምነት ስለሆነ የግንኙነቱ ተፈጥሮ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል።

ወንዶች ሚስቶቻቸውን እንደ እግዚአብሔር ቃል ማክበራቸው የሚረጋገጠው ጾታዊ ጥቃትን በሴቶች ላይ ከማድረስ ሲቆጠቡ እና እንዳይደርስ ሲከላከሉ እንዲሁም ለሌሎች አርአያ የሚሆን የመከባበር እና የመተማመን ትዳር ሲኖራቸው ነው፡፡

52

፭ እንክብካቤና ድጋፍ

ሀ) ዐውድ

ኤች.አይ.ቪ በደማቸው የሚገኝ ወገኖች ተገቢውን እና አስፈላጊውን የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆን ረዥም እና ጤናማ የሆነ ሕይወት ለመኖር ይችላሉ። ይህንን ለማድረግም እንክብካቤና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ይህም የሕክምና ድጋፍን፣ የተመጣጠነ ምግብ መመገብን፣ እረፍት ማድረግን፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግን እንዲሁም ማኅበራዊ እና የስነ-ልቡና ድጋፍ ማግኘትን ይጨምራል። ሰዎች የደረሰባቸውን ችግር በተሻለ ሁኔታ መቋቋም የሚችሉት የሌሎችን ድጋፍ ካገኙ ነው። እንዲያ መሆኑም አዎንታዊ አቋም እንዲኖራቸው ያግዛል።

አብዛኛውን ጊዜ ኤች.አይ.ቪ በደማቸው የሚገኝ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ያህል ድጋፍ አያገኙም። ይህም ከተለያዩ ምክንያቶች የመነጨ ይሆናል። ለምሳሌ፦ አንድ ሰው የሕክምና እርዳታ እንደሚያስፈልገው አያውቅ ይሆናል። ስለዚህ ሁሉም ሰው በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የኤችአይቪ ምርመራ በማድረግ ቫይረሱ በደሙ

53

ውስጥ መኖሩን እና አለመኖሩን ማወቁ ጠቃሚ ነው። ነገር ግን ሰዎች ተገቢውን የኤችአይቪ ምርመራ እንዳያደርጉ ከሚያደርጉአቸው ምክንያቶች መካከል የምርመራ ውጤታቸውን በማወቃቸው በኅብረተሰቡ ሲገለሉና መድልዎ ሲደርስባቸው በማየታቸው ነግ በኔ በማለት እንዳይመረመሩና ውጤታቸውን እንዳያውቁ ትልቅ እንቅፋት ይሆንባቸዋል፡፡

ለችግር የተጋለጡ ህጻናት እና ኤች.አይ.ቪ በደማቸው የሚገኝባቸው ወገኖች ከሕክምና እርዳታ ያለፈ ድጋፍ እና እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል። ግለሰቦች እና ቤተሰቦችም እንዲሁ ማኅበራዊና ስነ-ልቡናዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። በተጨማሪም ሌሎቹ የቤተሰብ አባላት በየራሳቸው መንገድ ችግር ሊገጥማቸቸው ስለሚችል ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። በአንዳንድ ሃይማኖታዊ ተቋማት ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ወገኖች እና ለችግር የተጋለጡ ህጻናት አሳዳጊዎች የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች በተመለከተ የሚወያዩበት መድረክ አላቸው፣ ሌሎች ደግሞ ለማኅበረሰቡ ስለ ቫይረሱ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ማኅበራዊ ስብሰባዎችን ያካሂዳሉ፣ እንደገናም ሌሎቹ ደግሞ የማኅበረሰቡን አቋም እና አስተሳሰብ ለመለወጥ ሲሉ ከሕክምና ባለሙያዎች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው ይሠራሉ።

የሃይማኖት መሪዎች ለችግር የተጋለጡ ህጻናት እና ኤች.አይ.ቪ በደማቸው ለሚገኝባቸው ወገኖች ድጋፍ እና እንክብካቤ እንዲያገኙ ለማስቻል ከፍተኛውን ሚና ይጫወታሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንደኛው መንገድ ኅብረተሰቡ በተሳሳተ አመለካከት ኤች.አይ.ቪ በደማቸው የሚገኝ ወገኖች ላይ የሚያደርሰውን አሉታዊ አመለካከት ማስቀረት እና ስለ ቫይረሱ የተሻለ ግንዛቤን በማስጨበጥ የማኅበረሰቡን አስተሳሰብ

54

መለወጥ ነው። በተጨማሪም ለችግር የተጋለጡ ህጻናት እና ኤች.አይ.ቪ በደማቸው የሚገኝባቸው ወገኖች አስፈላጊውን ድጋፍ ማለትም የትምህርት ድጋፍ፣ የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት እና የስነ-ልቡና ድጋፍ ፍላጎት ያሉትን እንዲያገኙ ማመቻቸት ይቻላል። ሁሉም ሰው ተገቢውን እንክብካቤ ማግኘቱን ለማረጋገጥ በኅብረተሰቡ ውስጥ ቡድኖችን ማቋቋም መልካም አካሄድ ነው።

55

ለ) መልዕክት

እያንዳንዳችን ልዩ ልዩ ችሎታዎች እና ስጦታዎች ያሉን ሲሆን ሌሎችን ለመደገፍ ልናውላቸው ይገባል። ኢየሱስ ክርስቶስ የእርሱን እንክብካቤና ድጋፍ የገለጠው የታመሙትን ሰዎች በመፈወስ ነበር። እኛም እንክብካቤና ድጋፋችንን በአካላዊው፣ ማኅበራዊው እና ስነ-ልቦናዊው አቅጣጫ ልናበረክት እንችላለን። ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከማኅበረሰቡ የተገለሉ ሰዎችን ወደእርሱ በማቅረብ ተገቢውን ድጋፍ እና እንክብካቤ አድርጓል፣ እኛም አርአያነቱን ልንከተልና ፍቅር እና ርህራሄያችንን ክርስቶስ እንዳደረገው ለሁሉም ልንለግስ ይገባል።

ኤች.አይ.ቪ እና ኤድስ በማኅበረሰባችን ላይ ፈተናን የሚጥል ሲሆን ከፈተናዎቹ አንዳንዶቹ ከአሉታዊ አስተሳሰብ እና በሌሎች ላይ ከመፍረድ የመነጩ ናቸው። ልክ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም ይህንን ሁኔታ ተቃውመን ሁሉም ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤና ድጋፍ ማግኘታቸውን ማረጋገጥ ይኖርብናል። ይህንንም ለማድረግ ትክክለኛውን መረጃ በመስጠት፣ አድልዎና መገለልን በማስወገድ እና በሌሎች ላይ መፍረድን በማስቀረት የሰዎችን አስተሳሰብ ለመቀየር መሥራት ይኖርብናል። ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በሥጋ ተገልጦ ያስተምር በነበረበት ጊዜ የተከሰተ ነገር ባይሆንም እንኳን ኤች.አይ.ቪ እና ኤድስን ከእግዚአብሔር ቃል አንጻር ልንረዳው ያስፈልጋል። እግዚአብሔር አንዳችን አንዳችንን እንድንወድድ ጠርቶናል ይህም ምንም ዓይነት አጥር የሌለው ሁሉን የሚደርስ ፍቅር ነው።

56

ሐ) መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶች

1. ለድሆችና ለድሀ አደጎች ፍረዱ ለችግረኛውና ለምስኪኑ ጽድቅ አድርጉ፤ብቸኛውንና ችግረኛውን አድኑ ከኃጢአተኞችም እጅ አስጥሉአቸው። (መዝሙር 82፥ 3-4)

2. ለድሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፥ በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል። (ምሳሌ 19፥ 17)

3. ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም (ማቴዎስ 9፥12)

4. ተርቤ አብልታችሁኛል፤ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል፤ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛል፤ ታርዤ አልብሳችሁኛል፤ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፤ ታስሬ ጎብኝታችሁኛል:: (ማቴዎስ 25፥ 35-36)

5. እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ሁሉ እናንተም ለእነርሱ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ የሙሴ ሕግና የነቢያት ትምህርትም የሚሉት ይህንኑ ነው። (ማቴዎስ 7፥12)

6. ጌታም ባያት ጊዜ አዘነላትና፦ አታልቅሽ አላት። (ሉቃስ 7፥ 13)

57

7. በመጨረሻው ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፤ የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ፥ እንደ ወንድሞች ተዋደዱ፥ ሩህሩኆች እና ትሁታን ሁኑ:: (1 ጴጥሮስ 3፥ 8)

58

መ)ዐውዳዊ ስብከት

ርዕስ:ለድሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፥ ምሳ.19፥17

ኢየሱስ ክርስቶስ ለታመሙት እንክብካቤ ያደረገው እነርሱን በመፈወስ ነው። የእርሱ ድርጊቶች ለዛሬ ኑሯችን ትልቅ ትምህርት ይሰጡናል። ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ከአድልዎና ከመገለል ጋር በተያያዘ በለምጽ በሽታ የተያዘን ሰው አገኘ። ክርስቶስም እጁን ዘርግቶ ሰውየውን በእጁ ዳሰሰና ፈወሰው። ይህ ሰው በደረሰበት ለምጽ ምክንያት በህብረተሰቡ ትልቅ መድልዎ እና መገለል እየደረሰበት የነበረ ነው፡፡ ነገር ግን ወደ ክርስቶስ ሲመጣ እንደሚያድነው እንደማያገለው በማመን ስለነበረ ክርስቶስም ፈውሶታል፡፡

እግዚአብሔር አንዳችን አንዳችንን እንድንንከባከብ እና እንድንደግፍ የጠራን ከመሆኑም ባሻገር ልንከተላቸው የሚገቡ ምሳሌዎችን አስቀምጦልናል። ʻተርቤ አብልታችሁኛል፤ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል፤ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛል፤ ታርዤ አልብሳችሁኛል፤ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፤ ታስሬ ጎብኝታችሁኛልʼ። እነዚህ ሁሉ በተግባር፣ ለሌሎች በሚደረግ እንክብካቤና ፍቅር አማካይነት የተገለጡ የፍቅር ሥራዎች ናቸው።

59

በማኅበረሰባችን መካከል ፈተና የገጠማቸው ሰዎች አሉ። እነዚህ ፈተናዎች የመጡባቸው ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ የተነሳ ሳይሆን እኛ ለእነርሱ ካለን አመለካከት የተነሳ ነው። አንዳንድ ጊዜ በሌሎች ላይ መፍረዳችን እና አስተሳሰባችን እንዲህ ያሉትን ሰዎች የሚጎዳ ስለሆነ ልንለውጠው ያስፈልገናል። ምክንያቱም ሰዎች ወደኛ የሚመጡት ወይም ችግራቸውን የሚያካፍሉን ከእኛ ለችግራቸው መፍትሄ መንገድ እንድናሳያቸው እንጂ ተጨማሪ ጭንቀት እና መገለል እንድናደርስባቸው አይደለም፡፡ ኢየሱስ ክርሰቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ይገለሉ ለነበሩ ሰዎች እንክብካቤ እንዳደረገ እንዲሁ፣ እኛም በዘመናችን መገለል ለደረሰባቸው ሰዎች እንክብካቤ እናድናደርግ አሳስቦናል እኔ እንደወደድኳችሁ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ በማለት።

እግዚአብሔር አንዳችን ለአንዳችን ርህራሄን እንድናሳይ እና እርስ በርስ ተዋድደን አንዳችን በሌላችን ላይ መፍረዳችንን እንድንተው ይመክረናል። እንዲሁም እግዚአብሔር በመቸገር ላይ ያሉትን፣ ድሆችን እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡትን እና ለችግር የተጋለጡ ህጻናትን ለማገዝ እንድንሠራ ይጠራናል። ድጋፋችንን እና እንክብካቤያችንን ልንሰጥ ያስፈልጋል። በፍጻሜውም እግዚአብሔር ለእነዚህ ድርጊቶች ሽልማትን የሚሰጥ ሲሆን መልካም ሥራን ለሠሩትም ሰዎች ዋጋቸውን ይከፍላል። እናንተ የአባቴ ብሩካን ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን ርስተ መንግሥተ ሰማያትን ውረሱ፤ ብራብ አብልታችሁኛል፣ ብጠማ አጠጥታችሁናል፣ ብታረዝ አልብሳችሁኛልና በማለት ለመልካም ሥራችን ተገቢውን ዋጋ ይከፍለናል፡፡

አዘጋጅ:- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ከዩ.ኤን.ኢድስ ጋር

በመተባበር የካቲት ፳፻፮ ዓ.ም